እውነት የአንድ ሰሞን ውሸት ነበረች!!
ሴትየዋ ታላቅ ከሚባሉት ደራሲዎች የምትመደብ ናት። ስራዎቿን አንብቦ የማያደንቃት የለም። ስትፅፍ የምታነሳቸው ሃሳቦች የገዘፉና ሰው መሆንን አብዝተው የሚሰብኩ ብቻቸውን የህይወት ስንቅ ናቸው።
ደስታና ሰላምን የሚሰብኩ ናቸው። ፍቅር፣ እውነት፣ እምነትና ፅናትን አርቅቃ ብትንትን ሀሳቦችን ገጣጥማ አንባቢዎቿን ማስደነቅን ፍፁም ተክናበታለች።
ይቺው የአንባቢዎቿን ቀልብ ማሸፈት ስራዋ ያደረገችው ደራሲ ከብዕር ስሟ በቀር ማን ትባል፣ የት ትኑር፣ ማን ትሆን የሚያውቅ የለም።
የአለም ታላላቅ ሚዲያዎችና ስመጥር ጋዜጠኞች ሳይቀሩ የሴትየዋን ማንነት አውቀው ለማወቅ ቢጥሩ አልተሳካላቸውም።
"ይህቺ ሴት ግን ማናት?! "
"ተነብበው የማይጠገቡ ድርሰቶች እያላት፣ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አድናቂዎችን አፍርታ፣ እንዴት ማንነቷን አልገጥ አለች? " የሚለው የብዙሃን ጥያቄ ነበር።
በዚህ መንገድ ስትኖር ከዕለታት በአንደኛው ቀን የኔ ከምትላቸውና ሚስጥሯን ጠብቀው ያሻትን ከሚያደርጉላት ቤተሰቦቿና ሁለት አብሯደግ ጓደኞቿ ገፍቶ የመጣ ጫና በረታባት።
"እድሜሽ እየሄደ ነው፣ ሴት ነሽ፣ አዲስ ህይወት ያስፈልግሻል፣ ትዳር መስርተሽ መኖር አለብሽ። " የሚል ተደጋጋሚ ሙግት።
እሷም ከብዙ ማፈግፈግ በኋላ ሀሳባቸውን ተቀብላ፣ ደጋግማም አስባበት መወሰኗን ነገረቻቸው። ወደ አዲሱ ሕይወቷም የሚያደርሳትን መንገድ አሰበች። ከተለመደው አኗኗሯ የተለየውን አካሄድም መረጠች።
ከሰዎች ጋር አትገናኝም፣ አትቀራረብም ነበር መገናኘትና መቀራረብ ጀመረች። ወዳጆች አፈራች። ከቤት የመውጣት ልምድ አልነበራትም ነበር ወጥታ ከጓደኞቿ ጋር መዝናናት፣ መጨዋወት፣ ሲኒማ ቤቶችን፣ የመዝናኛ ስፍራዎችን መዞር ጀመረች። በዚህ መልኩ ያለመችውን ለማሳካት ስትል ብዙ ደከመች። ብዙ ጣረች። ግን አልተሳካላትም።
ሀብት እና ዝና ቢኖራትም ቆንጆ ሴት አልነበረችም። ጥበብን እንጂ ወንድ ልጅን አማልሎ የሚያስቀር ውበት፣ ከአይን የሚገባ ቁመናን አላደላም። ጥሩ አልባስ፣ ውድ ውድ ጌጣጌጦቿን ብታደርግ፣ ቀንና ማታን ዘንጣ ሽክ ብላ ብትወጣም ስራዬ ብሎ የሚያያት አልተገኘም።
ተፈተነች። ሁሉም ነገር ታክቷት በአጭር ጊዜ ለሽንፈት እጇን ሰጠች። ሁሉም አስጠላትና መሰልቸት ውስጥ ስትገባ ያዩ የቅርብ ሰዎቿ ሁለት ምርጫ ያለው ምክር ለገሷት።
አንደኛዋ ዝናዋን እንድትጠቀምበት እና ከሚሊየን አድናቂዎቿ መሃል በራሷ መንገድ እና በራሷ መስፈርት የሚስማማትን መርጣ ማግባት እንደምትችል ስትነግራት
ሌላኛዋ ደግሞ ያሻትን ማድረግ የሚያስችላት ሀብት ስላላት በገንዘቧ በዘርፉ ታዋቂ የሆነ ዶክተር ተመርጦ በዘመናዊ ቀዶ ህክምና መዋብ እንደምትችል እና በውበቷም የተማረከውን ማግባት እንደምትችል የሚጠቁም ነበር።
ሁለተኛው ሀሳብ ገዛት። ጊዜ ሳትወስድ የትና እንዴት የሚለውን አጣርታ፣ ቀጠሮ ይዛ በቀናቶች ውስጥ ከሁለቱ ጓደኞቿ ጋር ተጓዘች። ባገኙት አድራሻ መሰረትም ወደ ሆስፒታሉ ሄደው፣ ከተባለው ዶክተር ተገናኝተው ለቀዶ ሕክምናዋ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ አደረጉ።
ተሳክቶላት ተቆነጀች።
ከማገገሚያ ጊዜዋ በኋላም የታከመው መልኳን እያየች ማመን አቃታት። ውብ ሆናለች። አብረዋት ያሉት ጓደኞቿም ጭምር እስኪገረሙ ድረስ ነበር ያማረችው።
ከዚህ ሁሉ አድካሚ ጊዜ በኋላ ደግሞ ይጨንቃት ገባ። ጭንከቷም አማርኩኝ ሳይሆን እንዴት ብዬ ነው ዳግም ወደኖርኩበት ማህበረሰብ እና ወደትውልድ ሀገሬ ተመልሼ የምኖረው የሚል ነበር።
እንዳታስበው ብዙ ነገሯም ነው። ተወልዳ ያደገችበት፣ ተምራ የከበረችበት፣ ቤተሰቦቿና የልብ ወዳጆቿ ያሉበት፣ ተወዳጅ ስራዎቿን ኖራ የሰራችበት ሆነባት።
ከብዙ ማመንታትና ማሰላሰል በኋላ ግን ሀገር ቀይራ መኖርን መረጠች። ጓደኞቿንም አመስግናቸው በለቅሶ ወደመጡበት ሸኝታቸው መኖር ወደ መረጠችበት ሀገር አመራች።
ለሀገሩም ለከተማውም አዲስ ነበረችና ተረጋግታ መኖሪያ ቤቷን ገዝታ ኑሮዋን እስክታደርግ በከተማው ላይ አለ የተባለ ሆቴል አረፈች።
በቀናት የሆቴል ቆይታዋም ስትገባ፣ ስትወጣ፣ ወደ ዋና ገንዳ ስትሄድ፣ መናፈሻው ላይ ተቀምጣ ስታነብ፣ ይመለከታት የነበረውን የሆቴሉን ባለቤት ቀልብ አሸፈተች።
በቁንጅናዋ ስለመማረኩም ፍንጭ አሳያት። ደጋግሞ አጠገቧ እየሄደ እንዳይከፋሽ፣ ብቸኝነት እንዳይሰማሽ እያለ መንከባከብ አበዛ። እንደምንም ቀረባት።
ተላመዱ፣ ተግባቡ፣ በደንብ ተቀራረቡ፣ ተዋደዱ።
ቤቱ ወሰዳት። መኖሪያውን ጎበኘችለት። እራት ጋበዛት። እንዲህ እንዲህ እያሉ ፍቅር፣ ሁለት ወር ባልሞላ እድሜም ፈጥነው ትዳር መስርተው መኖር ጀመሩ።
ወራት፣ አመት እያሉ ኖረው ፍቅራቸውን የሚያቆይላቸው ወንድ ልጅ ወለዱ።
በዚህ ጊዜም ፍቅራቸውን የሚረብሽ፣ መስማማታቸውን የሚያፈርስ ጥል መምጣት ጀመረ። የጥላቸው መነሾ ልጃቸው ነበር።
ባል "እኔንም አንቺንም የማይመስል ልጅ ተቀብዬ እንዴት ነው አባት ተብዬ የምኖረው?" ሲል
እሷ ደግሞ " እመነኝ ያንተ ልጅ ነው " ትለዋለች።
ቀን አለፈ። መጨቃጨቅ፣ መነታረክ በዛ። ይህ ነገር ትዳሬን ሳያሳጣኝ በፊት እውነታውን ሳላስቀር መንገር አለብኝ አለች።
መልከ ጥፉ እንደነበረች፣ በህክምና ጥበብ እንዳማረች፤ ደስተኛ ህይወት እንደነበራት፣ ምርጫ ስላልነበራትም ቀዶ ህክምናውን ልታደርግ እንደተገደደች፣ ልጃቸውም የቀደመው መልኳን ይዞ እንደተወለደ. . . አንድ በአንድ እውነታውን ልታስረዳው ሞከረች።
በሰማው ነገር ተደናግጦ ማመን አቃተው። ግን እውነት መሆኑን ቢያረጋግጥና የቀድሞውን ፍቅሩን እንደሚሰጣት ጭምር ነገራት።
እሷም የነገረችውን አምኖ መቀበል ካልቻለ በራሱ መንገድ ሊያረጋግጥ እንደሚችል የሆስፒታሉንና የዶክተሩን ሙሉ አድራሻ ሰጠችው። ደውሎም አረጋገጠ።
አሁንም አልተዋጠለትም ። አንድ ቀን ምሽት ላይ። እራት እያሰናዳች ሳለ፣ ድንገት ከመሬት ተነስቶ በብስጭት ሊናገራት ወዳለችበት ሄደ። ዘወር ብላ አየችው። መልኩ ተቀያይሯል፣ ስሜታዊ ሆኖም ነበር። በፍርሃት ተመለከተችው። በግራ እጁ የተገለጠ መጽሐፍ ይዟል።
" አንቺ ግን ለምንድነው እውነቱን የማትነግሪኝ ? " ብሎ ጮኸባት። " እውነት እኮ አንድ ሰሞን ላይ የነበረችው ውሸት ናት ።" ስትለው ደነገጠ። በፍጥነት ገልጦ የያዘውን መጽሐፍ ተመለከተ። የተናገረችውን ቃል በቃል በሚያነበው መጽሐፍ ላይ ተጽፎ አየው። አሁንም ተገረመ። ከሷ ጋር ተኮራርፎ የሚያነበው መጽሐፍ የራሷ ድርሰት ነበር።
ሁሉንም ነገር ነገረችው። በህይወቱ ባገኛቸው ብሎ ከሚያስባቸው ሰዎች ፊተኛዋ እሷ ነበረች። የሰማውን እውነት ማመን አልቻለም። እኮ እንዴት. . .?!
የሚሊየኖችን ህይወት መቀየር የቻለችው ሴት ሚስቱ ናት። ያውም የልጁ እናት።
ግን እንዴት?!
የሚሊየኖችን ህይወት መቀየር የቻለች ሴት በራሷ መተማመን ያቃታት ለምንድን ነው?
የአለም ሕዝብ አድንቆ የማይጠግባት፣ ከልጅ እስከ አዋቂው የሚያጨበጭብላት፣ ደራሲ ትክክለኛው ማንነቷን ማሳወቅ ለምን አልፈለገችም? ራሷን ለምን ደበቀች ?
ጥበቧስ ምን ነበር ?
የምትጽፈውን ህይወት ስለምን መኖር አቃታት?
ከምትፈጥራቸው ገፀ-ባህሪያትስ ለምን አነሰች?
ከጥያቄዎቹ እኩል በቆመበት ፈዝዞ ያያታል።
ሚስቱን ያወቃት ዛሬ ገና ነበር።
Minase Ab Wako